ጄኔራል ሰዓረ መኮንን

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረቡት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥያቄ የማቅረብ መብት ቢኖራቸውም የሄዱበት መንገድ ግን መመሪያን ያልተከተለ፣ ኢ - ሕገ መንግስታዊ ድርጊትና ሰራዊቱን የማይወክል ነው ብለዋል፡፡


የመከላከያ ሰራዊቱ የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ስራ በብቃት ሲወጣ እንደነበርና ሰራዊቱ በአገሪቱ ተከስቶ የነበሩትን ግጭቶች ለመፍታት የሄደበት ሁኔታ ጥበብ የተሞላበትና ውጤታማ ነበር ብለዋል ጄኔራል ሰዓረ፡፡

ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የሁለተኛ የኮማንዶ ክፍለ ጦር አባላት በርካታ ግዳጆችን በብቃት ሲወጡ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፣ ከኑሮ ጋር ተያይዘው የቀረቡት ጥያቄዎች ተገቢ ቢሆኑም የሄዱበት መንገድ ግን አግባቢነት የለውም ብለዋል፡፡

ይህንን ድርጊት ከኋላ ሆነው የገፉት፣ ያደራጁት አካላት በቁጥጥር ስር የዋሉ አሉ፣ በቀጣይም እርምጃ እንደሚወሰድ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ገልጸዋል፡፡