የፍስሀ ተገኝ የቤተሰብ ፍለጋ ጉዞ

ፓስፖርቱ ላይ የትውልድ ስፍራ የሚለው ክፍት ቦታ ላይ 'ሐረር' ተብሎ ተጽፏል። የተወለደው ግን ሐረር አይደለም። ታዲያ ለምን ሐረር ተብሎ ተጻፈ?

በእርግጥ ሐረር አሳድጋዋለች። ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ሰጥታዋለች፤ ለፍስሀ ተገኝ።

የፍስሀ ህይወት በጥያቄዎች የተከበበ ነው። 'ቤተሰቦቼ፣ ዘመዶቼ ወዴት አሉ?' የሚለውን ጥያቄ እንዳነገበ ከሐረር አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ እንግሊዝ ባዝኗል።

የ1997 ዓ. ም ምርጫ የሚወደውን የስፖርት ጋዜጠኛነት ብቻ ሳይሆን ሀገሩንም አሳጥቶታል። ያኔ ኤፍኤም አዲስ 97̏. 1 እየሰራ ሳለ አዲስ አበባ በ97ቱ ምርጫ ማግስት ታመሰች።

በወቅቱ ህይወታቸው ካለፉ ሰዎች አብዛኞቹ የተገደሉት ባንክ ለመዝረፍ ሲሞክሩ ነበር የሚል ዜና እንዲያነብ ተሰጠው፤ አሻፈረኝ አለ። ህሊናዬ የማያምንበትን ነገርስ አልናገርም ማለቱ ሥራውን አሳጣው። የኋላ ኋላ ከትውልድ ሀገሩ መሰደድ ግድ ሆነበት።

የሥጋ ዘመዶቹን የማግኘት ፍላጎቱን እንዳነገበ ወደ እንግሊዝ አቀና። ለጥያቄው መልስ ሳያገኝ በዓመት ላይ ዓመት ተደረበ።

በ2010 ዓ. ም ያልተጠበቀ ዜና ተሰማ። በተለያዩ ሀገሮች በፖለቲካ ጥገኝነት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደሀገራችሁ መመለስ ትችላላችሁ ተባሉ።

ጥሪውን ተቀብለው ከአስርታት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን ለመርገጥ ከቻሉ አንዱ ፍስሀ ነው። 2011 ዓ.ም ለመቀበል ባትወልደውም ወዳሳደገችው ከተማ ወደ ሐረር አቀና።

«ቤተሰቦቼን ማግኘት አለብኝ. . . »

ያደገው ሐረር ኤስኦኤስ የህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ነው። የልጆች ማሳደጊያው ውስጥ ለአስር ህጻናት አንድ እናት ይሰጣል። ፍሰሀን ከሌሎች ዘጠኝ ልጆች ጋር ያሳደጉት እናት አሁን ጡረታ ወጥተዋል።

«በጣም የምወዳት የማፈቅራት እናቴ እሷ ነች። የምወደው ቤትም ኤስኦኤስ ነው፤ አሳድጎኛል። ቤተሰብ ጎደለብኝ ሳልል አድጌያለሁ» የሚለው ፍስሀ አዲሱን ዓመት ከእናቱ ጋር ማሳለፉ እጅጉን አስደስቶታል።

ሆኖም የዘመናት ጥያቄው ማቃጨሉን አላቆመም።

«ቤተሰቤ የታሪኬ አካል ነው፤ የአብራኬ ክፋዮች ናቸው። መፈለግ አለብኝ። ማግኘት አለብኝ፤»

ስደት ቤተሰቦቹን እንዳያፈላልግ አግዶት ነበር። ቤተሰቦቹን ሳይገኝ የባከኑ ዓመታት ቢቆጨውም ለማንነት ጥያቄው መልስ ለማግኘት ወደ ላሊበላ ተጓዘ።

የተወለደው ላስታ አካባቢ እንደሆነ ቢያውቅም፣ እትብቱ የተቀበረበትን ቦታ በትክክል አያውቅም። የሥጋ ዘመዶቹ የት እንዳሉም መረጃው የለውም።

እሱና እናቱ በ77ቱ ረሀብ ሳቢያ ወደ ወለጋ፤ ቄለም ተወሰዱ። ቄጦ የሚባል ሰፈራ ጣቢያ ይኖሩም ነበር። እናቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ከአርባ ልጆች ጋር ወደ ኤስኦኤስ ተወሰደ።

«እዚያ ስናድግ ቤተሰባችን፣ ወላጃችን፣ አሳዳጊያችን፣ እናታችን፣ አባታችን ኤስኦኤስ ነበር። ሙልቅቅ አድርጎ ነው ያሳደገን» ይላል ስለአስተዳደጉ ሲናገር።

እድሜው እየጨመረ ሲሄድ ስለቤተሰቦቹ ማንነት ያለማቋረጥ ያሰላስል ጀመር። ለጥያቄው መልስ የሚሰጥ ኢሜል እጁ ሲገባ ለፍለጋው መንገድ ተቀየሰለት። ኢሜሉ ለኤስኦኤስ የተሞላ ቅጽ ሲሆን፤ የትውልድ ቦታውን እንዲሁም የእናቱን ስም ከነአያታቸው ይዟል።

ከእንግሊዝ ከተመለሰ በኋላ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ስለቤተሰብ ፍለጋው ያወራ ነበር። ይህን የሰማ አንድ ሰው እናቱ የላስታ ሰው ስለሆኑ በፍለጋው ሊያግዙት እንደሚችሉ ይነግሩታል።
«አባቴ አለ!»

ወደ ላሊበላ በረረ። እኚያ ሴት ቤትም አረፈ። ደስታ ይባላሉ። ፍስሀ ወደ ላሊበላ ከመሄዱ በፊት የቤተሰቦቹን ማንነት እያጣሩለት ነበር። «ለመሆኑ የእናትህን አያት ስም ታውቃለህ?» አሉት። «ቢሰውር ይባላል፤ ሙሉ ስሟ ሸዋዬ ታገል ቢሰውር ነው» ሲል መለሰ።

ደስታ ጊዜ ሳያጠፉ ወደ አንድ ሰው ደወሉ። የደወሉለት ሰው የነገራቸው ነገር እሳቸውንም ፍስሀንም በሀሴት የሞላ ነበር።

«ሙጃ የሚባል ቦታ ለሚገኝ ተድላ ለሚባል ሰው ደውላ የእናቱ አያት ስም ቢሰውር ነው ስትለው፤ የቢሰውር ቤተሰቦችማ የኛ ቤተሰቦች ናቸው አለ። ከዛ በደስታ ጨፈረች፤ እኔንም አቀፈችኝ፤»

በማግስቱ ከላሊበላ ወደ ሙጃ ሄደ። ከዚያማ የዘመድ ጎርፍ አጥለቀለቀው።

«በእናቴም በአባቴም በኩል የተገኙ ሰዎች ነበሩ። እነሱን ካገኘን በኋላ እነሱ ሌሎችን ይዘው ማምጣት ጀመሩ። ቀጥሎም ሙጃ ውስጥ ወንድም አለህ ተባልኩ»

ፍሰሀ ለእናቱ ብቸኛ ልጅ እንደሆነ ነበር የሚያውቀው። ታናሽ እህቱ ሞታለች። ወንድምህ የተባለው ሰው የአባቱ ልጅ ነበር። እዚያው ሙጃ ውስጥ የሚኖረውን ወንድሙን ሲያገኘው፤ አስቦትም አልሞትም የማያውቀውን ብስራት አሰማው።

«አባታችን በህይወት አለ!»

መላ ህይወቱን አባቱ እንደሞቱ ነበር የሚያስበው። ኢሜል የተደረገለት ቅጽ ላይም አባቱ መሞታቸው ተጽፏል። ወደ አባቱ ስልክ ደውሎ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጻቸውን ለመስማት በቃ።

«የተወለድኩት ብርግነት ነው»

ፓስፖርቱ ላይ 'ሐረር ተወለደ' ይባል እንጂ እትብቱ የተቀበረው ብርግነት ነው።

ልጅ ሳለ እናቱን እና እሱን ከትውልድ ቀያቸው የሸኛቸው የእናቱ ታናሽ ወንድም ነበር። «እሽኮኮ አድርጎ ሸኘኝ» የሚለውን አጎቱን ዳግም አገኘ። ከበርካታ የእናቱ ወገኖች ጋርም አገናኘው።

«የእናቴን እህቶች፣ አክስቶቼን አገኘሁ። የእነሱን ልጆች፣ የልጅ ልጆች አገኘሁ። የእናቴ ታናሽ ወንድም፤ አጎቴ ጋር ሄጄ አራት ቀን ቆየሁ። ስልክ የለ፣ ኤሌክትሪክ የለ፣ የገጠር ህይወትን ለመድኩ። በግ ታርዶልኝ ሲያሞላቅቁኝ ነበር።»

የእናቱ ታላቅ እህት ትርንጎ ይባላሉ። አብዛኞቹ ዘመዶቹ 'ሞቷል' ብለው ቢያምኑም፤ እሳቸው ግን 'በህይወት አለ' ይሉ ነበር። ይጸልዩለት እንደነበርም ይናገራል።

እንዳፋቸው ሆኖ በአይነ ሥጋ ሲያገኙት 'ትተኸኝ አትሂድ' ብለውት እንደነበር በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል። እሱና አክስቱ የተነሱትን ፎቶ በትዊተር ገጹ ሲለጥፍ ተከታዮቹ በፍጥነት ነበር ምላሽ የሰጡት።

የቤተሰብ ፍለጋ ጉዞውን ከጀመረበት እለት አንስቶ ትዊተር ገጹ ላይ ይጽፍ፣ ፎቶም ይለጥፍ ነበር። አብረውት ያሉ ያህል ጉዞውን በድረ ገጽ የተከታተሉ ወዳጆቹም መልካም ምኞታቸውን ይገልጹለት ነበር።

የልጅነት ትውስታውን ከአክስቱ ከሰማ በኋላ በስልክ ድምጻቸውን የሰማውን አባቱን በአካል ለማግኘት ወደ ሳንቃ ሄደ።

«አባቴ ካገኘኝ ጀምሮ ሲያለቅስ ነበር የዋለው» ይላል ፍስሀ። ሳንቃ ውስጥ ያገኘው አባት ብቻ ሳይሆን በአባት የሚገናኛቸው እህትና ወንድም ጭምርም ነበር።

«ሙጃ አንድ ታላቅ ወንድም ነበረኝ። ከእሱ ተጨማሪ አንድ እህትና አንድ ወንድም አገኘሁ»


ጉዞውን ሲጀምር አባት፣ እህት፣ ወንድም፣ አክስት፣ አጎት አገኛለሁ ብሎ አልነበረም። በስተመጨረሻ ግን ራሱን በዘመድ ተከቦ አገኘው። የሆነው ሁሉ ቢያስደስተውም እንደዘገየም ተሰምቶታል።

እሱ ቤተሰቦቹን ለማግኘት በተቻለው ሁሉ ጥሯል። ነገር ግን 'እነሱስ ለምን ሊፈልጉኝ አልሞከሩም?' ብሎ ግን ይጠይቃል።