ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል መልቀቂያ አስገቡ፡፡  


ፓርላማው ዛሬ በነበረው 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የቀረበለትን አዳዲስ የካቢኔ አባላት ሹመት ያጸደቀ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ የአፈ ጉባኤዋን የስራ መልቀቂያ ተቀብሏል፡፡ 

ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ከአፈ ጉባኤነታቸው ቢለቁም፤ የሰላም ሚኒስቴር ተብሎ በአዲስ መልክ የተቋቋመውን መስሪያ ቤት በበላይነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተሾሙት ወ/ሮ ሙፈሪያት፤ አዲሱ የስልጣን ቦታቸው ቁልፍ ከሚባሉት የመንግስት የስልጣን እርከኖች መካከል አንዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡ 

‹‹የሰላም ሚኒስቴር›› በሚል ስያሜ የተቋቋመው አዲሱ መስሪያ ቤት፤ በጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ተቋማትን በበላይነት የሚቆጣጠር ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ብሎም በአጎራባች ሀገሮች ሰላም እና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የማድረግ ኃላፊነትም አለበት ተብሏል፡፡

በወ/ሮ ሙፈሪያት የሚመራው ይኸው መስሪያ ቤት፤ የፌዴራል ፖሊስና የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከልን ጨምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳን) እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን በበላይነት እንደሚቆጣጠር ወይም እንደሚመራ ታውቋል፡፡

እነዚህ መስሪያ ቤቶች ተጠሪነታቸው ለዚህ መስሪያ ቤት እንደሚሆን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም፤ በቀድሞ አጠራሩ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር የሚባለው መስሪያ ቤት ስልጣን እና ተግባር በሰላም ሚኒስቴር ስር ይጠቃለላል ተብሏል፡፡

ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ባስገቡት የስራ መልቀቂያ ዙሪያ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ለፓርላማው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በማብራሪያቸውም አፈ-ጉባኤዋ መልቀቂያ ያስገቡት በስራ መደራረብ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  

አፈ ጉባኤዋ ባለፉት ጊዜያት በነበራቸው የምክር ቤቱ ቆይታ ለውጥ ማምጣታቸውን የገለጹት ዶ/ር ዐብይ አህመድ፤ ‹‹ከኃላፊነታቸው የሚለቁት በስራ መደራረብ እንጂ በብቃት ማነስ አይደለም፡፡›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ 

ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ሲሾሙ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ-ዴኢህዴን ሊቀ-መንበር እንዳልነበሩ፣ አሁን ግን የፓርቲው ሊቀ-መንበር በመሆናቸው የስራ መደራረብ ጫና እንዳረፈባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር ዐብይ አህመድ በአፈ ጉባኤዋ የስራ መልቀቂያ ዙሪያ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ፤ ‹‹ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ካላቸው ድርብ ኃላፊነት የተነሳ ሙሉ ጊዜ በመስጠት መስራት ስለማይችሉ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውንና ምክር ቤቱ ጥያቄያቸውን ይቀበል ዘንድ ጠይቀዋል፡፡ 

የፓርለማው አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በኋላ፤ የአፈ ጉባኤዋን የስራ መልቀቂያ በሙሉ ድምጽ ተቀብለዋል፡፡ በወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ቦታ አዲስ አፈ ጉባኤ በቅርብ ጊዜ እንደሚሾም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡  
ዶ/ር ዐብይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከመጡ በኋላ ባዋቀሩት አዲስ ካቢኔ ውስጥ ከተካተቱ ተሹዋሚዎች መካከል ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አንዷ ሲሆኑ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ከተሾሙ ወደ ዘጠኝ ወር ገደማ ይሆናቸዋል፡፡  

ወ/ሮ ሙፈሪያት አፈ ጉባኤ ሆነው የተሾሙት በቀድሞዉ አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ቦታ መሆኑ ይታወሳል፡፡