ፈራሁ ~ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)


ፈራሁ 
ቴዎድሮስ ካሳሁን 

(ቴዲ አፍሮ)

💚💛❤️💚💛❤️




ደመናት በሰማይ ቅርጽ እየተፈጠሩ አይስሉም ትተዋል፣
የጓሮ ሰበዞች አበቦች እረግፈዋል፡፡ 

ወፎችም ጠፍተዋል እንደ ድሮ አይመጡም፣
ሽማግሌዎች ዛፍ ስር ሸንጎ አይቀመጡም፣
ያልጠኑ ጥጃዎች እየፈነጠዙ መስክ ላይ አይሮጡም፣
ልጆች ሲቆጧቸው ቶሎ አይደነግጡም፣
ህጻናት አውቀዋል እንደልጅ አይፈሩም፣
በእሳት ዙሪያ ከበው ተረት አያወሩም፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አይባልም ቀረ፣
ያልኖረውን እድሜ ልጅም እየኖረ፡፡
ወንዞችም ደርቀዋል እያሉ አይፈሱም፣
ወጣቶች ደክመዋል ለሽበት አይደርሱም፣
ክረምትና በጋም ተናፍቀው አይመጡም፣
ቀኖቹ እሮጠዋል ምንም ጊዜ አይሰጡም፣

እየገሰገሰ እንዲህ እየጋለበ ጊዜ በቀን ፈረስ ዘመን ቢያስስም፣
በዓመት በዓል ቀን እንኳን ዓመት በዓል አይደርስም፣
አሁን እንደድሮ አሁን ያለ አይመስልም፣
ቀብር ይፋጠናል ለቅሶ አይደረስም፡፡

መርዶ አይተረክክም ሞትም አይፈራ፣
በሠርግ ቤት እንኳን አይሞቅም ጭፈራ፡፡
ለአደራ የሚበቃ ሰው አንሷል በአገሩ፣
ጎረቤት አይመጣም ጠንክሯል አጥሩ፡፡

እናቶች በፍቅር ቡና አይተጣጡም፣
ምን አገባኝ እያሉ የሰው ልጅ አይቀጡም፣
ሁሉም ነገር ቢኖር በቃ! ምንም የለም፣
ጥም አይቆርጥም ውሃ አይማርክም ቀለም፣
ገበታ ላይ ያለም እህል ቆርሶ ይዞ መተከዝ አያጣም፣

ይሰከራል ቶሎ በወግ አይጠጣም፣
በቃ!! በቃ!! ደስታ የለም፣ 
በቃ!! ምንም የለም፡፡ 
ምኞትም ተመኘ የድሮውን ነገር፣
ጠቅሎ ሄደና ሀገር ከራሱ ሀገር፡፡

አብሮ መብላት ቀርቶ ፍቅር የጠፋ ዕለት፣
ደስታም ይጨክናል ተስፋም ይጨፍናል፣
የፊቱ አይታይም አሁን ይደፈናል፣
መልኩ አይናገርም ተፈጥሮም ዝም ይላል፣
ሙሉ ሕይወት የለም ሁሉም ባዶ ባዶ፣ ባዶ ባዶ ይላል፣
አሁን የኛም ነገር ይህንን ይመስላል፣ 
ግን ተስፋ አለ ሁሉም ነገር ጥሩ ይሆናል፡፡

ህዳር 2001 ተፃፈ!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ፍቅር ያሸንፋል!!